ቢሊየነሩ ጃክ ዶርሲ አዲስ ያልተማከለ የብሉቱዝ መልዕክት መተግበሪያ ይፋ አደረገ።

ቢትቻት (#BitChat) ተብሎ የሚጠራው ይህ አዲስ መተግበሪያ፣ በአሁኑ ወቅት በሙከራ ላይ ሲሆን በአፕል (Apple) ቴስትፍላይት (TestFlight) በኩልም ተደራሽ ሆኗል። ቢትቻት ተጠቃሚዎች ያለምንም ኢንተርኔት ወይም የበይነመረብ ግንኙነት መልዕክት እንዲለዋወጡ የሚያስችል ያልተማከለ እና በአቻ ለአቻ (peer-to-peer) ቴክኖሎጂ ላይ ተመስርቶ የሚሰራ መተግበሪያ ነው። ዋና አላማውም ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ግላዊነትን የጠበቀ እና ከሳንሱር ነፃ የሆነ ግንኙነትን ማስቻል ነው።

መተግበሪያው ሙሉ በሙሉ የሚሰራው ያለ በይነመረብ፣ ያለ ሴሉላር ኢንተርኔት አገልግሎት አልፎ ተርፎም ሲም ካርድ ሳያስፈልገው በብሉቱዝ ሜሽ ኔትዎርክ (Bluetooth mesh network) አማካኝነት ብቻ ነው።

የቢትቻት (BitChat) ቁልፍ ገጽታዎች፦
ኦፍላይን ግንኙነት፦ ሙሉ በሙሉ በብሉቱዝ የሚሰራ በመሆኑ በይነመረብ አያስፈልገውም።

ያልተማከለ አሰራር፦ የተጠቃሚዎችን መረጃ የሚያከማች ወይም የሚያነብ ማዕከላዊ ሰርቨር የለውም፤ ይህም ግላዊነትን ያረጋግጣል።

ስም- አልባነት፦ ለመመዝገብ ኢሜይል፣ ስልክ ቁጥር ወይም አካውንት መክፈት አያስፈልግም።

ሙሉ ምስጠራ (End-to-End Encryption)፦ ሁሉም መልዕክቶች በከርቭ25519 (Curve25519) እና ኤኢኤስ-ጂሲኤም (AES-GCM) የደህንነት ደረጃዎች የተመሰጠሩ ናቸው።

የተራዘመ የክልል ሽፋን፦ መተግበሪያው በአቅራቢያ ያሉ ሌሎች መሳሪያዎችን እንደ ማስተላለፊያ በመጠቀም የመልዕክት መላኪያ ርቀቱን እስከ 300 ሜትር እና ከዚያ በላይ ያራዝማል።

ዓለም እና የሰው ልጆች በተለይ በግሎባላይዜሽን ሰበብ የተከፈተባቸውን የመረጃ ደህንነት ስጋት እና የፋይናንስ ነፃነት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተዋጉ ያሉበትን ሁነት እየተመለከትን ነው። ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ: ጊዜ ከፈጣሪ ቀጥሎ መልሱን ሰጪው አካል የሚሆን ይሆናል።